ጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቀቀ፤
የጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል ለጀማሪ ተመራማሪዎች በዳታ አያያዝ፤ ትንታኔና አር/R/ ሶፍትዌር አጠቃቀምዙሪያያተኮረ ስልጠናን ከኢትዩጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ማዕከላት እና በብሔራዊ ደረጃ ከክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ለመጡ የተለያዩ በግብርና ምርምር ስራ ላይ ለተሰማሩ ተመራማሪዎች በማዕከሉ መሊኮ ስብሰባ አዳራሽ ከመጋቢት 27 ቀን 2013 ዓ.ምጀምሮ እስከ ሚያዝያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን የነበረውን ስልጠና በዛሬው ዕለት አጠናቋል፡፡
ይህ ስልጠና በጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል በብሔራዊ ቡናና ሻይ ምርምር ፕሮግራም እና በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከጂኦስፓሻልና ባዮሜትሪ ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን በዘርፉ ልምድ ያላቸው ተመራማሪዎች ስልጠናውን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡
አቶ ለሚ ቤክሲሳ በጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የብሔራዊ ቡናና ሻይ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ በስልጠናው ላይ እንደተናገሩት የአገራችንን የዕድገት ጉዞ ለማሳካት ግብርና በቀዳሚነት ኃላፊነት የተጣለበት ዘርፍ መሆኑን ገልፀው ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ማዕከሉ አዳዲስ የለውጥ ስራዎችን በማከናወን፣ ችግሮችን በመፍታት የተመራማሪውን አቅም ለመገነባትና ብሎም በእውቀት ላይ የተመሰረቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሰለጥኑ በማድረግ ረገድ መጠነ ሰፊ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው፤ በተለይም እንደ ቡና ያሉ ከራሚ ሰብሎች ብዙ ጥንቃቄዎችን የሚፈልጉ ስለሆነ በዚህ ረጅም ጊዚያት ውስጥ የሚሰበሰቡ መረጃዎችን ተመራማሪወቻችን በቀላሉና በሰለጠነ አሰራር በአግባቡ ያደራጁና መተንተን ይችሉ ዘንድ ይህን ስልጠና መውሰዳቸው በእጅጉ ያግዛቸዋል ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው መረጃን እንዴት እንደሚሰበስቡ እና እንደሚተነትኑ ብሎም ተግባራዊነቱ ምን መምሰል እንዳለበትና እንዴት ተቀናጅቶ መሰራት እንደሚገባ የጋራ ግንዛቤ መያዝ የሚያስችል ሆኖልናል ያሉ ሲሆን በተጨማሪም እርስ በርስ በመማማር የተሸለ ልምድ እንድንቀስም ስልጠናው እረድቶናል ብለዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ በሚደረጉ ምርምሮች እንደሀገር የተሻለ ብቃት ያለው እና ተወዳዳሪ የሆነ ተመራማሪን ለማፍራት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ወሳኘ ናቸው፡፡ በመሆኑም በእውቀት ላይ የተመሰረተና ጊዜውን የዋጀ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችል ብቁ ተመራማሪን መፍጠር የሁሉንም ትብብርና ድጋፈ የሚፈልግ ሂደት መሆኑ ታዉቆ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊያግዙ ይገባል፡፡ ሌላው በተናጠል የሚደረጉና የተቆራረጡ ስልጠናወች ወጥነት ባለውና በተቀናጀ ሁኔታ ቢሰጡ እንደሀገር በግብርናው ዘርፍ ብቁ ተመራማሪዎችን ለማፍራት ይረዳልና በጋራ የመስራቱ ሂደት ቢኖር መልካም ነው እንላለን፡፡ ተመራማሪውም በበኩሉ የቀሰመውን እውቀት ወደመሬት አውርዶ በመስራት ሀገራዊ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባዋል፡፡