ኢንስቲትዩቱ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አከበረ
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሰራተኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ110ኛ በአገራችን ደግሞ ለ45ተኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በእንስቲትዩቱ ዋናው መስሪያ ቤት ህሩይ አዳራሽ ”በኮቪድ-19 ተጽዕኖ ውስጥም የሴቶች የአመራር እኩልነትን ማምጣት” በሚል መሪቃል ተከብሮዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የግብርና ኤክስቴንሽን ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረሰ ተሾመ የመግቢያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በመግቢያ ንግግራቸውም ላይ እንደምርምር ተቋም ቀኑን ስናከብር ሴቶች በመሀበራዊ ኑሮ፤ በኢኮኖሚና በምርምሩ ዘርፍ ያበረከቱትን ሁለንተናዊ ሚና በመዘከር ነው ብለዋል፡፡ ወደ ፊትም ሴቶች ያለባቸውን የቤተሰብ ጫና በማቃለል በምርምሩ ወደፊት እንዲመጡ በመደገፍ ወደመሪነት ለማብቃት ማገዝ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን፤ በተጨማሪም ሴቶችን ማክበር ብሎም እራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ለራስ አጋዣ መፍጠር እናራስን ማክበር ነው ብለዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የስርአተ ጾታ ምርምር አስተባባሪ የሆኑት ወይዘሮ ለምለም አበበ ደግሞ የዘንድሮውን የሴቶች ቀን ስናከብር ከሌላው ጊዜ በተለየ ነው ያሉ ሲሆን ይኸውም ካለብን የስራ ሀላፊነት በተጨማሪ የኮቪ19 ወረርሽኝን በመቋቋም ቤተሰባችንን እና መሀበረሰባችንን ከወረርሽኙ ለመታደግ ብሎም ስርጭቱን ለመግታት ተጨማሪ ትጋትና ጉልበት በተጠየቅንበት ወቅት ላይ ማክበራችን ነው ብለዋል፡፡አያይዘውም እንደምርምር ተቋም ሴቶችን በዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክህሎት በማጎልበት በአመራር ቦታ በእኩልነት ማሳተፍ ለሀገር እድገት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ጨምረውገልጸዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ በኮሚዩኒኬሽን ዳይሬተር ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ባሲሊዎስ መነሻ ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን ከበአሉ ታዳሚዎች ጋር የፓናል ውይይት ተካሂደዋል፡፡ በውይይቱም ላይ በስርአተ ጾታ ዙር ያ የግንዛቤ ማስበጫ ስራ በመስራት ፤ የተለያዩ የድራማ እና የስነ-ጽሁፍ ዝግጅቶችን በማድረግ ተከብሯል፡፡
በመጨረሻም በዓሉን በየጊዜው ቀኑን ጠብቆ ማክበር ብቻ ሳይሆን በሀገራችን ሴቶች ያሉባቸውን የመብት፤ የእኩልነት፤ የሀብትና የሰላም እጦት ችግሮችን በመፍታት መሆን ይኖርበታል፡፡ ለሴቶችና ህጻናት ነገን የተሻለ ለማድረግ ሁልጊዜ እና በየትኛውም ቦታ ድህነት እና ችግርን በማጥፋት ልንሰራ ይገባል ፡፡ ሌላው የሴቶችን የበታችነት የማይቀበል ብሎም ጠለፋና አስገድዶ መድፈርን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡ መንግስት እና ባለድርሻ አካላት ብሎም እያናዳናዳችን ሰላም ለሴቶች እና ህጻናት ያለውን ዋጋ በመረዳት ለእናቶቻችን፤ ሴት ልጆቻችን እና እህቶቻችን ስንል ሁላችንም እንደዜጋ የበኩላችንን ለማበርከት ሀላፊነት አለብን፡፡ የዕለቱ መልእክት ነው፡፡