የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል የምርምር ጅማሮ
ወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም በምርምር ስራዎቹ ከ 508 ሄክታር በላይ በኩታ ገጠም አስተራረስ በጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ እና ሽንብራ በማሳ ላይ በማስተዋወቅ እንዲሁም አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም ከአምስት አመት በላይ ያለምንም ምርት የቆዩ ማሳዎችን ወደ ምርታማነት እያሸጋገረ ይገኛል፡፡ የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ከማስተዋወቅና ከማፍለቅ ጎን ለጎን ከነባር ማዕከላት ውጤታማነታቸው የተረጋገጡና ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በማምጣት የማላመድ እና በማባዛት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡
ማዕከሉ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን እና በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ በጥቅሉ ከ 826 በላይ ወንድ አርሶ አደሮች እና 143 ሴት አርሶ አደሮችን በኩታገጠም የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ቴክኖሎጂዎችን ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን ማዕከሉ ከወልቂጤ ዩንቨርስቲ ጋር በጋራ በመሆን የማላመድ፣ የዘር ብዜት እንዲሁም የሙከራ ስራዎችን የሚከናወኑበትን ቦታ በማመቻቸት እየሰራ ይገኛል፡፡ የብርና አገዳ (በቆሎ)፣ የቅባት እህል (ኑግ፣ ተልባ)፣ ባቄላ እና ዋና ዋና ሰብሎችን (ጤፍ፣ ስንዴ፣ገብስ) ከተለያዩ ነባር የምርምር ማዕከላት በማምጣት የሙከራ ስራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በቀጣይም ማዕከሉ የምርምር አድማሱን በማስፋት ዝርያዎችንም በመጨመር ያልተዳረሱ ቦታዎች ለማደረስ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡
የታዩ የምርምር ማሳዎች
በጎሮ ወረዳአዳሚ ዋዴሳ ቀበሌ ላይ የተሰራ 30ሄክታር የሚሸፍን ኩታገጠም የጤፍ ማሳ ሲሆን 64 ወንድ እና 4 ሴት አርሶአደሮች ተሳትፈውበታል፡፡ ተጠቃሚ አርሶአደሮቹ የምርምር ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና አለመጠቀም ልዩነትን በሰብሉ አያያዝ በቀላሉ መለየት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከግብርና ተመራማሪዎች ያገኙት ስልጠናና፣ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ክትትል በምርት ሂደቱ ላይ ለውጥ እንዳመጣ ተናግረዋል፡፡
88 ወንድ እና 18 ሴት አርሶ አደሮችን ያሳተፈው የበኢዛህ ወረዳ ጎደብ ቀበሌ በአርሶአደሮች ዘንድ ብዙ ተሞክሮዎችን ያስገኘ ነው፡፡ መሬታቸው አሲዳማ በመሆኑ ምክንያት ለ አመታት ምንም አይነት የሰብል ምርት ማምረት ያልቻሉ ሲሆን በዘንድሮ ከምርምር ጋር በጋራ በመሆን አሲዳማ አፈሩን በኖራ በማከም 36 ሄክታር ላይ በኩታ ገጠም ስንዴንና ገብስን ማምረት ችለዋል፡፡
በሶዶ ወረዳ ሶሎቄና ሪፌንሶ ቀበሌ ስንዴን በኩታ ገጠም በመስመር በመዝራት 52 አርሶ አደሮችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በዚህም 40 ሄክታር የሚሸፍን ሲሆን በአካባቢው ከተዘሩ ቴክኖሎጂ ከማይጠቀሙ አርሶ አደሮች ማሳ ጋር ሲነጻጸር የምርምር ስርአቱን ተከትሎ የተዘራው የተሸለ መሆኑን መመልከት ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ በደቡብ ሶዶ በአገምሳ ቀበሌ የተከናወነ ጤፍን በመስመር በመዝራት ቴክኖሎጂን በመጠቀም በ30 ሄክታር ላይ ማምረት ችለዋል፡፡ በዚህም 49 ወንድና 9 ሴት አርሶ አደሮች ተሳትፈውበታል፡፡
ማዕከሉ በስፋት ካከነወናቸው የሰብል የቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ ስራዎች ውስጥ አንዱ ጤፍ ነው፡፡ በእንዳገኝ እና ቸሀ ወረዳ በአጠቃላይ 124 አርሶ አደሮችን ያሳተፈ ጤፍን በኩታ ገጠም በመዝራት 62 ሄክታር ያዳረሰ ስራ ተከናውኗል፡፡ ከምርምር ባለሙያዎች መስማት እንደቻልነውም በቸሀ ወረዳ በአዘርና ሲሲ ቀበሌ የሚገኙ በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት ከዩንቨርስቲ የተመለሱ ወጣት ተማሪዎች ወደ 12 ሄክታር የወል መሬት በመውሰድ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቁንጮ ጤፍን አምርተዋል፡፡ በዚህም ለአካባቢው ነዋሪዎች ተጨማሪ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡
አሲዳማ አፈርን በማከም ከስንዴ በተጨማሪ ጤፍን በኩታ ገጠም አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገ ስራ በ ጣጤሳ፣ አምበልታ እና ማመዴ ቀበሌዎች ተሰርቷል፡፡ በዚህም 51 ወንድ እና 1 ሴት አርሶ አደር 40 ሄክታር የሚሸፍን የጤፍ ምርትን ማምረት ችለዋል፡፡ በተመሳሳይ በእነሞር እና ኢነር ወረዳ በ 20 ሄክታር ላይ ከ 50 በላይ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ ጤፍን ኩታ ገጠም አምርተዋል፡፡
ምርጥ ተሞክሮዎች
ü በመስክ ጉብኝት ወቅት በጎደብ ቀበሌ ማሳ ላይ የታየው ምርጥ ተሞክሮ እንደሚያሳየው እንዲሁም በአርሶ አደሮች ለመግለፅ እንደተሞከረው አካባቢው በአሲዳማ አፈር የተጠቃ በመሆኑ ከአምስት አመት በላይ ምርት መሰብሰብ አለመቻላቸውን ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ግዜ ከወልቂጤ ምርምር ማዕከል ጋር በጋራ በመሆን መሬታቸውን በኖራ በማከም ስንዴ እና ገብስን በ36 ሄክታር ማሳ ላይ በኩታ ገጠም ማምረት ችለዋል፡፡ አርሶ አደሮቹም በዚህ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ü በተመሳሳይ በቸሀ ወረዳ በኮቪድ 19 ምክንያት ከዩንቨርሲቲ የተመለሱ ተማሪዎች የወል መሬት በመውሰድ ከአጠቃላይ 62 ሄክታር ላይ 12 ሄክታር በመውሰድ ቁንጮ ጤፍን አምርተዋል፡፡