COVID-19 Response
 

የምግብ ዋስትናችን….. ከምድራችን

በዱብቲ…..አስቦዳናደበል….ገረኒ (ዴትባሀሪ)አፋምቦና አሣይኢታ ወረዳዎች የተካሄደ የመስክ ቀን በዓል 

የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል የ 2013 ..  የመስኖ ቴክኖሎጂ ማስተዋወቅና ማስፋፋት የመስክ ቀን በዓል መጋቢት 25 ቀን 2013 ..በአፋር ክልላዊ መንግስት በአፋምቦ እና ዱብቲ ወረዳዎች አካሄደ፡፡  እንደሚታወቀው ማዕከሉ የመስኖ ስንዴ ቴክኖሎጂ ምርምርን ከጀመረ አስርት ዓመታት ቢያስቆጥርም አሁን ላይ ከአስር በላይ የቆላ ስንዴ ዝርያዎችን በማውጣት ለመላው ኢትዮጵያ የቆላ እና የመስኖ ስንዴ  አምራቾች በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡የክልሉ ከፊል አርብቶ አደር ምርምር ኢንስቲትዩት ከፊል አርብቶ አደሮችን በክላስተር በማደራጀት ፣ከወረር ምርምር ማዕከል ጋር በጥምረት እና በቅርበት በመስራት የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም የተለያዩ ምክረሃሳቦችን በመቀበና ተግባራዊ በማድረግ ከፊል አርብቶ አደሮች ውጤታማ መሆን እንደቻሉ ገልጿል፡፡

 ወረር የምርምር ማዕከል የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ቢያቀርብም ከመንግስት በዋናነት ሁለት  ነገሮችን እንሻለን የሚሉት የክልሉ ከፊል አርብቶ አደር ምርምር ኢንስቲትዩት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዓሊ ሲሆኑ በዋናነት የመሠረተልማት መስፋፋት ማለትም ዘመናዊ የመስኖ ሲስተም እና ሜካናይዜሽን ቢሟሉ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ምንዛሬ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ በተቻለ መጠን መቀነስ፣ በመቀጠልም ሙሉ በሙሉ መሸፈን እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡ በአፋምቦ ወረዳ ከ4ዐ ሄ/ር መሬት ላይ የመስኖ ስንዴ ልማት የተሠራ ሲሆን 23 ከፊል አርብቶ አደሮች እንደተሳተፉ አቶ አሊ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል በዋናነት ትኩረት አድርጎ የሚሠራባቸው ሰብሎች ጥጥ፣ በቆሎ፣ ሩዝ እና ስንዴ ሲሆኑ በሰብሎች ላይ ምርምር በማድረግ ክልሉን እንዲያግዝ የምርምር ሙከረ የሚደረግበት መሬት እንደሚዘጋጅና እንደሚሰጥ አቶ ዓሊ ቃል ገብተዋል፡፡

 ዕለቱን አስመልክቶ አቶ ሽመልስ ዓለማየሁ የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ባደረጉት ንግግር ማዕከሉ ከአፋር አርብቶ አደር ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር የመስኖ ስንዴ ሙከራዎችን ከ2006 ዓ.ም.  ጀምሮ በከፊል አርብቶ አደር ማሣዎች ላይ በማልማት ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ማስፋፋት ስራ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ከውጭ የሚገባውን የስንዴ መጠን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት ከዚያም በዘለለ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ስንዴ ለማቅረብ የምትችልበትን አቅም ለመፍጠር ማዕከሉ መጠነ ሰፊ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ ማዕከሉ በዚህ ዓመት ሰፊ የመስኖ እርሻ ልማት ለመሥራት ዕቅድ ቢይዝም በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ምክንያት እንደታሠበው መራመድ እንዳልተቻለ አቶ ሽመልስ በስፋት ገልፀዋል፡፡ ማዕከሉ ከባለሙያ ድጋፍ ጀምሮ በርካታ ግብዓቶችን በማቅረብ እና በማስተባበር  1230 ሄክታር በላይ በአፋር ክልል የስንዴ ልማት ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ሲገልፁ ይኸውም በተለያዩ ወረዳዎች፣ ቀበሌዎች እና ከአርብቶ አደር፣ ከፊል አርብቶ አደር እና ከፍተኛ ባለሀብቶች ማሣ ላይ እንደሆነ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

 ዶ/ር ታዬ ታደሰ በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ምርምር ዳይሬክተር እና የአፋር ክልል የመስኖ ስንዴ ክላስተር አስተባባሪ የመስኖ ስንዴ ልማትን በክልሉ እዚህ ለማድረስ ከፍተኛ ርብርብ እንደተደረገ እንዳለ ገልፀው ለወረር ግብርና ምርምር ማዕከል፣ ለክልሉ አርብቶ አደሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡  ተቋሙ ቴክኖሎጂ ከማመንጨት ጀምሮ በአርብቶ አደሮች ፍላጎት በመፍጠር፤ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽ እንዲሆኑ እየሠራ እንደሚገኝ እንዲሁም ምክረ-ሃሣብ በመስጠት እና የመነሻ ዘር በማቅረብ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ እንዳለ ዶ/ር ታዬ ገልፀዋል፡፡ የመስኖ ስንዴ መነሻ ያደረገው የአፋር ክልል መሆኑን እና አሁን ላይ ወደ ሌሎች ክልሎች መስፋፋቱን ሲገልፁ ትልቅ ተነሣሽነት እና ኃላፊነትን ወስደው እዚህ ያደረሱ የወረር ምርምር ማዕከል ሠራተኞችን በድጋሚ አመስግነዋል፡፡    

 ዶ/ር ታዬ በክልሉ በቋሚነት እና በተደጋጋሚ የሚጠየቀውን የመሠረተ-ልማት አውታር ጥያቄ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባ ሲገልፁ በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ቁርጠኝነት እየታየ በመሆኑ ባለሀብቱም ተረባርቦ ያለውን የውኃ እና የመሬት አቅም አሟጦ መጠቀም እንደሚባ ገልፀዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም. የምርት ዘመን 40 ሺ ሄክታር ሊለማ ታስቦ በተፈጥሮ በተከሰተው የጎርፍ ችግር ሙሉ በሙሉ መተግበር ባይቻልም በ2013 ዓ.ም. አገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን 30 በመቶ ስንዴ ማግኘት እንደተቸለ ይኸውም 4.5 ሚሊዮን ዶላር የአገሪቱን ወጭ መታደግ የሚችል መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

 የአፋር ከፊል አርብቶ አደር ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ  ሙሐመድ አሚን የስንዴ ማሣ አጨዳውን በኮምባይነር አስጀምረዋል፡፡ የአፋር መሬት ዳቦ ነው፤ ሁሉም ከተረባረበ ውጤት ይመጣል፡፡ የምግብ ዋስትናችን….. ከምድራችን የሚሉት አቶ ሙሐመድ በቆላ ስንዴ ልማት ከመላው አገሪቱ የአፋር ክልል የአንበሣውን ድርሻ እንደሚወስድ ገልፀው ለወረር ግብርና ምርምር ማዕከል፣ ለግብርና ሚኒስቴር እና ድጋፍ ላደረጉላቸው አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ሁለተኛው የመስክ ቀን ምልከታ በአፋምቦና አሣይኢታ ወረዳዎች የተከናወነ ሲሆን የመስኖ ስንዴ ፕሮጀክት አስተባባሪው ዶ/ር ዳንኤል ሙለታ እንደገለፁት በመጀመሪያው ዙር በ2012 ዓ.ም.  170 ሄክታር መሬት በ2ኛው ዙር ማለትም በ2013 ዓ.ም. ደግሞ ከ270 እስከ 300 ሺ ሄክታር መሬት የመስኖ ስንዴ በማልማት እስከ 8.5 ሚሊዮን ሄክታር ስንዴ ለማምረት መታቀዱን ገልፀው ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት 50 በመቶ ለመሸፈን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ፤ መሸፈን እንደሚቻልም ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ35 ኩ/በሄክታር  በላይ ምርት ማግኘት እንደሚቻል እንዲሁም አንዳንድ ቦታዎተ እስከ 80 ኩ/ሄ መስጠት የሚችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ ገልፀዋል፡፡ አርብቶ አደሩ የመስኖ ስንዴ አመራረት ስልትን እያወቀ እና እየተረዳ መምጣቱን ተገንዝበናል ያሉት ዶ/ር ዳንኤል የመስኖ ስንዴ ከዝናብ ስንዴ ጋር ሲወዳድር ከምርት ብዛትም ሆነ ከጥራት አንፃር የተሻለ እንደሆን በስፋት አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር ዳንኤል የመስኖ ስንዴ ልማት ተሣታፊ ለሆኑ አርብቶ አደሮችን እና ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ምስጋና ሲያቀርቡ ለመጭው የምርት ዘመንም አስፈላጊው ዝግጅት የተፋሰስ እና የመሬት ዝግጅት ከወዲሁ እንዲደረግ አሣስበዋል፡፡ የመስኖ እና የሜካናይዜሽን ችግሮችንም ከመንግሥት ጋር በመሆን መቀረፍ እንዳለበት አፅንዖት በመስጠት አስገንዝበዋል፡፡ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትም በዋናነት በአርብቶ አደሮች ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት መፍጠር እና ቴክኖሎጂ በማቅረብ ልማቱን ሲያፋጥን የክልሉ መንግሥት በጀት መድቦ፣ ከፊል አርብቶ አደሮችን በማህበር አደራጅቶ ብድር በመጠየቅ ችግሮችን መቅረፍ የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት የመስኖ ስንዴ ልማትን ያስቀጥለዋል የሚል እምነት ያላቸው ዶ/ር ዳንኤል ዳቦ ላይ ቆመን ዳቦ ተቸግረናል በማለት በቁጭት ተናግረዋል፡፡

አቶ ሙሴ ያሲን የአሣይኢታ ወረዳ የእንስሣት፣ የእርሻ እና የተፈጥሮ ሃብት ሃላፊ… የመስኖ ስንዴ እርሻ በአፋምቦና በአሣይኢታ ወረዳ 2 ዓመታት ማስቆጠሩን ሲገልፁ በ213 ዓ.ም. የምርት ዘመን ሴቶችንና ወጣቶችን በማስተባበር በ180 ሄክታር መሬት ላይ ሥራው መጀመሩን ይኸውም በሄክታር ከ37 ኩንታል በላይ… ሊገኝ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡  በወረር ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሚቀርቡትን አዳዲስ ቴክኖሎጂ ማህበረሰቡ ተቀብሎ እንዲያስቀጥል ክልሉ እና ባለድርሻ አካላት ሊያግዝ እንደሚገባ አቶ ሙሴ ያሲን ሲገልፁ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ተወጥቶ የተሻለ ነገር እንዲገኝ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የተሻለ ነገር ለማድረግ የወረዳው መንግስት፣ የክልል እና የፌዴራል መንግስት አጠቃላይ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና ማህበረሰቡን በግብዓት መደገፍ እና መሠረተ-ልማት ማጠናከር የተፈጥሮ ሃብቱን በአግባቡ እንዲጠቀም ሁሉም የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት በማለት አሳስበው የመስክ ቀን ምልከታው ተጠናቋል፡፡

የኮምባይነር፣ የማዳበሪያ አቅርቦት የውኃ ብዙ ሰው የስራ ዕድል አግኝቷል፡፡ ውኃ በቂ ውኃ በሚያስፈልገው ጊዜ የውኃ አቅርቦቱን ካሟላን ጥሩ ስንዴ ማግኘት እንችላለን፡፡ ውኃ ሲኖረው ወደ መስኖ እንዲመጣ ካናል ያስፈልግል፡፡ ውኃ ሲበዛ ጠፍተናል፡፡ የመስኖ አውታር ችግር፡፡ አዋቭ ጠረጋ ያስፈልገዋል፡፡ ውኃ አጥተንም ባዝነናል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሊያስተካክልልን ይገባል፡፡